አለመኖር
A Book By - ዶር ዳዊት ወንድማገኝ

In Stock
አለመኖር
Available Book Type
|
|
📗Printed
Book Info
Author - ዶር ዳዊት ወንድማገኝ
Category - ልብወለድ (ስነልቦናዊ), ስነልቦናዊ psychological
Translated Book - No
Language - Amharic
Number of Pages - 374
Book Review
መነበብ ያለበት መፅሐፍ ‹‹አለመኖር!››
(እ.ብ.ይ.)
‹‹አለመኖር›› መፅሐፍ በዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ተፅፎ በ2009 ዓ.ም. ነው የታተመው፡፡ ይሄን መፅሐፍ ዘግየት ብዬ ነው ያነበብኩት፡፡ በውስጡ የተለያዩ ሃሳቦች አጭቆ የያዘና እኛነታችንን መለስ ብለን እንድናይ የሚያደርገን፣ እውነተኛውን አኗኗራችንን የሚያስጎበኘን፣ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን በሕይወታችን ላይ ትላልቅ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን እንድናስተውል የሚረዳን፣ መምሰልን ሳይሆን ራስን መሆንን የአዕምሮ ሰላም እንደሚያስገኝ የሚያስገነዝበን፣ እያንዳንዱ ገፀባህሪ የተወከለበት ስብዕና ማንነታችንን ቁልጭ አደርጎ የሚያሳይና የራሳችንን ደካማ ጎን ለይተን እንድናውቅ የሚያመራምረን፣ ከፍ ያለ ሃሳብ የተሸከመ፣ ጥልቅ ፍልስፍናዎችንና ረቂቅ አተያዮችን ያካተተ፣ በታማሚና አስታማሚ፤ በሃኪምና በታካሚ መካከል ያሉ አስተሳሰቦች፣ አመለካከቶች እንዲሁም ውዥንብሮችን አጥርቶ የሚያሳይ መቸቱን በዋና ከተማችን ሸገር ላይ የመሰረተ የልብወለድ መፅሐፍ ነው፡፡
‹‹አለመኖር›› ለክብሩ የሚጨነቀውን ዶክተር ‹‹ክብሩ››ን ያስተዋወቀን፣ ለደስታው የሚኖረውን መምህርና ዶክተር ‹‹ደስታን›› ያሳየን፣ የጠበቃዋ ሰብለን፣ የእነዶክተር ውቢትን የልብ ውበትን፣ የአዕምሮ ቁንጅናን አጉልቶ ያስመለከተን፤ የልጅነት ዕውቀትን፣ የአዋቂነት ጥፋትን ያስረዳን፣ አለመኖርን ከመኖር ጋር እያቃረነና እያመሳሰለ የዘረዘረልን፤ኑሮን በሰምና ወርቅ የሚተነትንልን፣ ያልተገለጠውን ድብቁን የማንነታችንን መጋረጃ የሚገልጥ፤ በየቤታችን ውስጥ ያለውን ጉድ ገሃድ አውጥቶ እንድንወያይበት ሃሳብ የሚሰጠን፤ በሃሳብ ጥግብ ያለ፣ በፍልስፍና የናጠጠ፣ ግሩም ድንቅ መፅሐፍ ነው፡፡
የዚህ መፅሐፍ ዋና ገፀባህሪ ዶክተር ‹‹ደስታ›› ይመስለኛል፡፡ ደስታ ኑሮን ቀለል አድርጎ የሚኖር፤ ለእያንዳንዷ ሃሳብ ለተሸከመች ቃላት ረቀቅ ያለ አተያይ ያለውና በተለመደ ንግግር የማያምን፤ ሃሳቡን የሚፈትሽ፣ አኗኗሩን የሚመረምር፣ እያንዳንዷ ድርጊቱን በየጊዜው የሚገመግም፣ አመለካከቱ ቀና የሆነ፤ አስተሳሰቡ ከፍ ያለ ሰው ነው፡፡ ደስታ ለደስታው የሚኖር እውነትን የሚከተል፤ ራሱን ሆኖ የሞተ የታላቅ ስብእና ባለቤት ነው፡፡ ከዚህ ገፀባህሪ የምንማራቸው ቁምነገሮች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡
አምላክ ሰውን ያህል የየራሱ ዓለም ያለው ልዩ ፍጡር ሲፈጥር የዚህ መፅሐፍ ደራሲ ደግሞ ዶክተር ደስታን የፈጠረበት ጥበብ ረቀቅ ያለ ነው፡፡ ደስታ አንስቶ የማይጥለው ሃሳብ የለም፤ ለየት ያለ አስተሳሰብ ያለው፤ ዓለሙን የሚታዘብ፤ ልምዱን በምክንያትና በማስረጃ የሚሞግት፣ የመኖርን ትርጉም የሚፈትሽ፣ ማንነቱን መልሶ መላልሶ በአዲስ ሃሳብ የሚገነባ ምርጥ ሰው ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከሰብለ ጋር መኪናቸውን ሽሮሜዳ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አቁመው እየተጨዋወቱ ወደእንጦጦ ተራራ በእግር ለማዝገም ጉዞ በጀመሩበት ጊዜ ሰብለ ወደኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብታ ተሳልማ ስትወጣ ደስታን በር ላይ አገኘችው፡፡ ወዲያው፡-
‹‹ምነው አልገባህም እንዴ?›› አለችው፡፡ እሱም ‹‹ንፁህ አይደለሁም›› አላት፡፡ ‹‹ለምን?›› ስትለው ‹‹የዋህነቴ ጠፍቶብኛል›› ሲላት ‹‹እንዴት?›› ብላ ጠየቀችው፡፡ እሱም‹‹ንጽህና በየዋህነት ነው የሚገኘው፡፡ እኔ ደግሞ የዋህነቴ በአዋቂነቴ ጠፍቶብኛል›› በማለት አስገራሚ መልስ ሰጣት፡፡
እውነት ነው አዋቂነት ንፁህነትን ማቆሸሺያ፣ ሰውነትን ማጥፊያ ጥይት ነው፡፡ ሰው እያወቀ ሲመጣ ሰውነቱን ዘንግቶ በገዛ ቢጤው ላይ ጨክኗል፡፡ የዋህነቱ ተነጥቆ፤ ሰው-ነቱ ተገፍፎ ቆዳ ብቻ ሆኗል፡፡ ማወቅ ቁስ ለመሰብሰብ ብቻ ነው የሆነው፡፡ ቀልብን የሚሰበስብ፣ መንፈስን የሚገዛ፣ ስሜትን የሚገራ፣ ፍላጎትን የሚገድብ ዕውቀት ማንም አይፈልገውም፡፡ የልጅነት ጥበብን ማንም ያስተዋለው የለም፡፡ ልጅነት ንፁህነት ነው፡፡ በልጅነት በትናንት ታሪክ አትጣላም፡፡ በልጅነት ጠቡ ወዲያው የሚረሳ ጊዜያዊ እንጂ ቋሚ አይደለም፡፡
በዚህ ዘመን እውነትን ተገን አድርገህ ለመኖር ከባድ ነው፡፡ ያልሆንከውን መስለህ እንድትኖር ነው ዓለሙ የሚጋብዝህ፡፡ ለሐቅ ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት፤ መኖር ወይም መሞት ምርጫ ያለበት የጦርነት ግንባር ላይ ራስን እንደማግኘት ሆኗል፡፡ የዓለም ጦርነት አዕምሮህን ነው የሚዋጋው፤ ጥይቱና ተኩሱ አስተሳሰብህ ላይ ነው፤ ማሸነፍ የሚፈልገው አኗኗርህን ነው፡፡ ልብህን መቀማት፣ ሰውነትህን መንጠቅ ነው የዓለሙ ውጊያ፡፡ ራስህን እንድትዘነጋ ትኩረትህን ወደውጪ ያደርግብሃል፡፡ ፍላጎትህ ገደብ አልባ እንዲሆንና በቁስ ፍቅር እንድትቃጠል ደመነፍስህን ይቆጣጠረዋል፡፡ አኗኗርህ መንጋው በለመደው የማስመሰል ህይወት ካልሆነ ከመንጋው ትለያለህ፡፡ ራስህን ተከትለህ ሕይወትህን የምትመራ ከሆነ ተነጥለህ ትመታለህ፡፡ አጨብጫቢ ካልሆንክ፣ ሕይወትህ ለየት ካለ፤ አስተሳሰብህ ከብዙሃኑ ከተለወጠ ጠላትህ ይበዛል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በመፅሐፉ ገፅ 5 ላይ ዶክተር ደስታ ለተማሪዎቹ የሰጠው ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹ካስመሰልክ ከሰው ጋር በሰላም ትኖራለህ፡፡ እምቢኝ ካልክ ትገለላለህ፡፡ በቤትህ፣ በጎረቤትህ፣ በመስሪያቤትህ፣ በሃገርህ ባዕድ ትሆናለህ፡፡ ይህ ማለት ግን በማስመሰልህ በሰላም ትኖራለህ ማለት አይደለም፡፡ በማስመሰልህ ከሌሎች ጋር ብትኖርም ለራስህ ግን ባዕድ ነህ፡፡ ከሰው መሃል ሆነህ ከራስህ ግን ተገልለሃል፡፡ እያንዳንዱ ድርጊትህ ከራስ ወይ ከሌላው ይለይሃል፡፡ ትልቁ የመኖር አጣብቂኝም ይሄ ነው፡፡››
አዎ! ማግኘት ማጣት የሰውን ሆዱን እንጂ ሕይወቱን አይለውጠውም፤ መልኩን ይቀይረው ይሆን እንጂ መንፈሱን አያድሰውም፡፡ ደስተኛ ሕይወት የሚገኘው በሆድ መጥገብ ብቻ ሳይሆን በነፍስም መርካት ነው፡፡ ብዙዎቻችን የማናስተውለው ነገር ይሄ ነው፡፡ ደስታን ለመሸመት ገበያ እንወጣለን፡፡ የዓለሙ ገበያ ደግሞ የተረጋጋ አይደለም፡፡ ሁሌም የደስታ ዋጋው እንደተሰቀለ ነው፡፡ ምክንያቱም ደስታን ከውጪ ለመግዛት እንጂ በቤታችን ለማምረት አንሞክርም፡፡ እውነተኛ ደስታ በተለያዩ የሃሳብ ግብዓቶች በራስ አዕምሮ ፕሮሰስ ተደርጎ፣ በልቦናችን የሚመረት የቤት ውስጥ ምርት (In-house product) ነው፡፡
ወዳጆች በመፅሐፉ የተነሱት ሃሳቦች የትየለሌ ናቸው፡፡ እዚህ ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ እፁብ ድንቅ የሆነ አተያዮች በመፅሐፉ ተሰግስገዋል፡፡ የሚፈለገው ረጋ ብሎ፤ ከራስ ጋር እየተከራከሩ፣ ሃሳቡን እያብሰለሰሉ፤ የሚሞገተውን እየሞገቱ፤ ሃሳብ ያነሰውን እየጨመሩ ማንበብ ብቻ ነው፡፡
መልካም ንባብ!
____________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
Digital/Audio Book Files
Br650.00