ሌላ ሰው Lela Sew

A Book By - ዶር ምህረት ደበበ Dr Mihret Debebe

In Stock

ሌላ ሰው Lela Sew

Available Book Type

|

|

📗Printed

Book Info

Author - ዶር ምህረት ደበበ Dr Mihret Debebe

Translated Book - No

Language - Amharic

Number of Pages - 440

Book Review

አንዳንድ ሃሳቦች ከ ‹‹ሌላ ሰው›› መፅሐፍ!
(እ.ብ.ይ.)
ዛሬ ጥቂት ሃሳቦቹን ተውሰን ሃሳቡን የምናብላለት መፅሐፍ ‹‹ሌላ ሰው›› የተባለ መፅሐፍ ነው፡፡ ይሄ መፅሐፍ ልቦለድ ሲሆን ደራሲውም ዶክተር ምህረት ደበበ ናቸው፡፡ መፅሐፉ በስድስት ክፍሎች ተከፋፍሎ በ451 ገፆች ተከሽኖ የዛሬ ሰባት ዓመት ሠኔ 2007 ዓ.ም ላይ የመጀመሪያ ዕትሙ ታትሞ አንባቢያን እጅ ገብቶ ብዙ ሰው አንብቦታል፤ እስከዛሬም እየተነበበ ይገኛል፡፡ ደራሲው በገፀባህሪያቱ በኩል ያስተላለፉልን መልዕክቶች የትየለሌ ናቸው፡፡ የመፅሐፉ ርዕስ የሆነው ዋና ገፀባህሪው ‹‹ሌላ ሰው›› የአባቱን ቃልና አደራ ለመጠበቅ ሲል የሚኖርበትን የባህር ማዶ የተመቸ ኑሮ ትቶ ወደሐገሩ በመመለስ በአዕምሮ ሐኪምነት ሙያው ሲያገለግል ይታያል፡፡ መፅሐፉ ያላነሳው ሃሳብ የለም፡፡ በተለይ ሰው ማንነቱ ተለዋዋጭ፣ እንደጊዜውና እንደአዋዋሉ እሱነቱ ተቀያያሪ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል፡፡
ልክ ነው! የሰው ልጅ መልኩ ብዙ ነው፤ ማንነቱ ሺ ነው፡፡ አንድን ሰው እንዲህ ነው ብለህ አትደመድመውም፡፡ ላንዱ ደግ ቢሆን ለሌላው ክፉ ይሆናል፡፡ አንዱ አዋቂ ቢለው ሌላው መሃይም ሊለው ይችላል፡፡ ሰውየው ራሱ ለየሰዉ የሚያሳየው ማንነት ወጥ አይደለም፡፡ ራሱን በሚገልጥበት ቦታ ሁሉ እሱነቱ የተለያየ ነው፡፡ ለዚህም አይደል ይኸው መፅሐፍ ክፍል ሶስት ገፅ 45 ላይ፡-
‹‹ሰው ሁሉ ሌላ ሰው ነው፡፡ ውጪው ሌላ፤ ውስጡ ሌላ! ኑሮው ሌላ ሕልሙ ሌላ፡፡ ልቡ ሌላ አፉ ሌላ፡፡›› …. የሚለን፡፡
አዎ! ሰው አንድም ሁለትም፣ ሶስትም፣ ሌላም ሌላም ፊት አለው፡፡ የዘንድሮ ሰው አክሮባቲስት ነው፡፡ ጊዜ እያየ አቋሙን ይለዋውጣል፤ ሰው እየለየ ማንነቱን ይቀያይራል፡፡ የዚህ ዘመን ሰው አብዛኛው ከሃሳቡ ጋር ያልተግባባ፣ ራሱን የዘነጋ፣ ለሚታየው የሚጓጓ እንጂ ለትክክሉ የሚኖር አይደለም፡፡ ሃይማኖቱ ያለው አፉ ላይ ነው፡፡ ‹‹ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያመልከኛል፤ ልቡ ግን ከኔ የራቀ ነው›› እንዲል ቅዱስ ቃሉ፡፡
እያወቀ የሚያጠፋ ሺ ነው፡፡ እቅዱን ያሳካ፣ አፉና ልቡን ያስማማ፣ ኑሮውና ህልሙን አንድ ያደረገ እምብዛም ነው፡፡ የዘመኑ ሰው ለአንዱ ቅዱስ ሲሆን ለሌላው አርኩስ ይሆናል፡፡ ደግነቱ መልክ አይቶ የሚያዳላ ነው፡፡ ፍቅሩን በገደብ ነው የሚገልፀው፡፡ ሁሉን ሰው በሰውነቱ በነፃ አይወድም፡፡ ለውለታው ውለታ ይጠብቃል፡፡ መልስ የሌለው ስጦታ አይሰጥም፡፡ ሁሉን በስሌት ነው የሚያደርገው፡፡ በካልኩሌሽን የሚንቀሳቀስ ትውልድ ማንነቱ ወጥ አይደለም፤ እንደየሁኔታው ሌላም ሌላም ሰው ነው፡፡ ትናንት ያሳየውን ማንነቱን ከደቂቃዎች በኋላ ይሽረዋል፡፡ ወረቱ ሲያልቅ እሱነቱ ይዋዥቃል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ ቃሉና ተግባሩን ቢያስማማ፣ እሱነቱን በአዳዲስ አስተሳሰብ ቢያዘምን፣ በዕውቀት ቢበለፅግ እሱም ይሰለጥናል ሐገሩንም ያሰለጥናል፡፡ ግለሰቦች ካልሰለጠኑ ሐገር አይሰለጥንምና፡፡ የግለሰብ መብትና ነፃነት ካልተከበረ መሰልጠን ስሙ እንጂ ግብሩ አይኖርም፡፡ የስልጣኔ ሀሁ እያንዳንዱ ዜጋ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የሚችልበትን ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ የአንድ ሐገር ብልፅግና ግለሰብና ማህበረሰብ ተኮር ካልሆነ ዋጋ የለውም፡፡ ለዚህ ነው ይኸው መፅሐፉ በገፅ 16 ላይ፡-
‹‹ሥልጣኔ የሚፈጠረው በግለሰብ ነፃነትና በማሕበረሰባዊ ሓላፊነት መካከል ባለው ሚዛን ላይ ነው፡፡ ግለሰብን እየገደሉ ሀገር ሀገር ማለት ቀልድ ነው፡፡ ሐገራዊ ኃላፊነትና ማንነትን እንደኳስ እየለጉ ነፃነትና መብት እያሉ ማላዘንም ትርጉም የለውም፡፡›› .. የሚለን፡፡
እውነቱን ለመናገር ያ ትውልድ ጊዜና ዕድል ገጥሞት የተረከባትን ሐገር የት እንዳደረሳት የአሁኑ ዘመን ገፈት ቀማሽ ትውልዶች ምስክር ነን፡፡ ታፍራና ተከብራ አንድ የነበረችን ሀገር ዛሬ ክብሯ ተገፍፎ፣ አንድነቷ ተሸርሽሮ፤ ህዝቧ በዘር ተከፋፍሎ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ እንዳለች ለማወቅ በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምዕራብም፣ በምስራቅም ያለውን የወገንን እልቂት፣ ርሃብና ቸነፈር ማየት በቂ ነው፡፡
በመፅሐፉ በገፅ 12 እንደተቀመጠው የ‹‹ሌላ ሰው›› አባትም እንደ ያ ትውልድ አባልነታቸው ቁጭታቸውን ለልጃቸው በግል ደብዳቤአቸው ገልፀውለታል፡፡
‹‹አሮጌውን ማፍረስ ላይ ስንረባረብ አዲሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄና ሃሳብ አላስጨነቀንም ነበር፡፡››
ሐቅ ነው! ማፍረስ ላይ የሰለጠነ ትውልድ ነው በሀገራችን በተከታታይ የተተካካው፡፡ ያለፈውን የመርገምና የተሰራውን የማውደም አባዜ እንደአዙሪት እየተመላለሰ ሐገራችንን ደቁሷል፡፡ ትናንት ገርስሶ በጣለውና በአሸነፈው ወዳቂ መንግስት መንገድ የሚጓዝ የዛሬው አገዛዝ ነገም የእሱ እጣ ፋንታ ውድቀት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ካለፈው የማይማር አመራር የትናንቱን ማፍረስ እንጂ ነገ በምን ዓይነት መንገድ ሐገሪቷን እገነባለሁ የሚል ብልሃትን አይዝም፡፡ የዛሬ ስልጣኑን እንጂ የነገ መድረሻውን አያስተውልም፡፡
አዎ ጊዜውን በበጎ፣ በዓላማና በስራ ያልተጠቀመ ግለስብም ይሁን መንግስት በጊዜ ይሸነፋል፡፡ ጊዜ ስጦታ ነው፤ ካልተጠቀምንበት ያከስረናል፤ ከተጠቀምንበትም ያተርፈናል፡፡ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የማይችል በዕድሜው ላይ እየቀለደ መሆኑን ይወቀው፡፡ አሁን ያባከንነው ጊዜ መቼም ቢሆን ተመልሶ አይመጣም፡፡ ደቂቃውን ወደኋላ ማዞር ፤ሰዓቱን ወደነበረበት መመለስ አይቻልምና፡፡
ለዚህ ነው ይኼው መፅሐፍ ከገፅ 34 እስከ ገፅ 35 ድረስ ስለጊዜ እንዲህ የሚለን፡-
‹‹በጊዜ ውስጥ ትናንት የትዝታ፤ ነገ ደግሞ የተስፋ ጎተራ ናቸው፡፡ ካመለጠ ትናንት.. ያልመጣ ነገ ይሻላል፡፡ በእጅ ያለ ዛሬ ግን ከሁሉም ይበልጣል፡፡ ዛሬ ሁሌም ያለ እየመሠለ የማይደገም… ተመልሶም የማይመጣ… ላንድ አፍታ ለቅጽበት ታይቶ ዳርቻ ከሌለው የዘላለም ጠፈር ገብቶ የሚሠወር… በትናንትና እና በነገ መሃል የተሸነቆረ እንቁ ነው፡፡ ‹‹ቅድም›› እና ‹‹በኋላ›› ግን ያለቦታቸው ዛሬ ውስጥ የተደነቀሩ የትናንትና እና የነገ ሽርፍራፊዎች ናቸው፡፡››
መፅሐፉ ቁምነገሩ ብዙ ነውና ያላነበበ ያንብበው! ያነበበም ይድገመው!
መልካም ንባብ!

Digital/Audio Book Files

    Br600.00

    The price displayed is for purchasing the book. If you choose to buy borrow the book for 7 days, the price will be reduced by 90%. By default, the "Borrow this book" option is selected.

    The book is available for borrowing. Select the number of days** the book can be borrowed. Standard borrowing duration is 7 days.
    Product total
    Options total
    Grand total
    -
    +

    ዶ/ር ምህረት ደበበ በሙያው የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት ነው። በየአመቱ ግማሽ ጊዜውን በኢትዮጵያ የቀረውን ደግሞ በአሜሪካ እየተመላለሰ ይሰራል። የመጀመሪያ መጽሃፉ “የተቆለፈበት ቁልፍ” በአስተሳሰብ ለውጥ ዙሪያ ያተኮረ ረጅም ልቦለድ ነበር። በዚህ “ሌላ ሰው” በተሰኘው አዲስ የረጅም ልቦለድ ትረካው ደግሞ ሥነልቦናንና ስብእናን የሚፈትሹ ግለሰባዊና ማህበራዊ አንኳር ጉዳዮችን እያነሳ ይጥላል። ረቂቅ የአእምሮ ጤና ችግሮችንም ይዳስሳል።
    መጽሃፉ በደረቅ ሃተታ የቀረበ ሳይሆን ስሜትና ስብእናን በተላበሱ የኛንው የሚመስል ኑሮና ታሪክ ባላቸው ገጸባህርያት የተሞላ ነው። በእነርሱ ሕይወት ነጸብራቅነት በውስጣችንና በአጠገባችን ያለውን ሌላ ሰው ያሳየናል። እያንዳንዱ ሰው በድርብርብ ማንነት የተለበጠ ስውር ስብዕና ያለው ሌላ ሰው ነው ይለናል። በእጃችን የያዝነውን መጽሃፍ ስናነብ በእጃችን የያዘውን ረቂቅ ስብእናችንንም የማንበብ ጥበብ ይሁንልን። ጸሃፊው ለአንባቢ መልካም ንባብን ለተነባቢም ጥልቅ መነበብን ይመኛል፡፡

    ሁሉም ሰው ሌላ ሰው… ሌላ ሰውም ሰው እንደኛው ሰው ነውና።