ተድባብ
A Book By - Hiwot Tefera / ህይወት ተፈራ

In Stock
ተድባብ
Available Book Type
|
|
📗Printed
Book Info
Author - Hiwot Tefera / ህይወት ተፈራ
Category - ታሪካዊ ልብወለድ
Publisher - walia books
Translated Book - No
Language - Amharic
Number of Pages - 369
Book Review
“አንዳንድ ግዜ ለገድል የሚጠሩት ግለሰቦች ይሆናሉ፣ ሌላ ግዜ ሕዝብ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው የኋለኛው ነው”
በዚህ ድንቅ አባባል የመጥሐፉን ጭብጥ አስይዛን ሕይወት ተፈራ ትቀጥላለች። ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ወረራ ለመመከት “እመራሃለሁ ተከተለኝ” ያሉት ህዝብ፣ “ታሪካዊና ገድላዊ ምላሽ ሰጣቸው። ከጥግ እስከ ጥግ ተነቃነቀ – የክብሩ ምንጭ የሆኑትን ሊያስጠብቅ፣ በማይመጣው በመጣበት ጠላት ላይ ክንዱን ሊያነሳ፣ የጋራ ታሪኩን ሊጽፍ፣ የታሪክ ተድባብ ላይ ሊወጣ።” ብላ በወኔ አነሳስታ፣ ተድባብ ለሚለው ቃል ገና ከጅምሩ ገፅ አንድ ላይ፣ የመፍቻውን አውድ አቀብላን ንባባችንን ትቀድልናለች።
ሕይወት ተፈራ በመጀመሪያ ከአንባቢዎች ጋር የተዋወቀችበትና ልባችን ውስጥ የቀረችበት፥ በራሷ እውነተኛ ታሪክ (የኢሕአፓ ተሳትፎዋ) ላይ ተመስርታ በጣፈችው “Tower in the Sky” (ማማ በሰማይ በሚል የተተረጎመ) መፅሐፏ ነው።
በማስከተልም፥ ሁለት ታሪካዊ ልብወለዶችን አበርክታልናለች። እነዚህም፥ Mine twin (ሃሰሳ በሚል የተተረጎመ) እና ምንትዋብ የተሰኙ ድርሰቶች ሲሆኑ፥ ሁለቱም ድርሰቶች ከታሪካዊ ልብወለድ ውስጥ የሚመደቡ ናቸውና ብዙ ልፋት፥ ጥናትና ምርምር ማድረግ ግድ ብሏታል። በጥንቃቄ ጥናት አድርጋ ለመፃፏም አንባቢያን መስክረውላታል። እነሆ አሁን ደግሞ “ተድባብ” በተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ ድርሰት ብቅ ብላለች። አሁንም ቢሆን፥ የገፀባህርያቱ አሳሳል የአድዋ ዘመቻና ጦርነትን ታሪካዊ ኩነት መከተሉ፥ ደራሲዋ በጥንቃቄ መሰረታዊ ጥናት አድርጋ የደረሰችው ስለመሆኑ የሚመሰክር ነው።
“ተድባብ”ን ስናነብ ውብና ያልተንዛዛ የቃላት ፍሰት ይዞን ጭልጥ ይላል። በእያንዳንዱ ገፅ አሰልቺ የምንለው አንቀፅ ስለማያጋጥመን፥ ለንባባችን እልባት ለማድረግ እንቸገራለን። ጭርስ ካላደረግን እረፍት የሚነሳን አይነት።
128 ዓመት ያስቆጠረውን የአድዋን ዘመቻና ድል ታሪካዊ ዳራ ሳይለቅ፥ ለአሁን ዘመን ሰው፥ በተለይ ወጣቶችን በሚስብ መልኩ ስለተፃፈ፥ ታሪካቸውን አያውቁም እየተባሉ ለሚወቀሱት ዘመናዊ ወጣቶች በጥበባዊ ስልት ታሪክ ማስገንዘቢያ ዘዴ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው። በኔ የልጅነት ዘመን ካራማራ፥ ጉርሱም፥ ኦጋዴንን የመሳሰሉ የምስራቁን የአገራችንን አካባቢዎች በምናብ የሚያስጎበኝ “የጣምራ ጦር” ድርሰት ትረካ በሬዲዮ ሰምተን አድገናል። በልባችንም ተቀርፆ በመቅረቱ፥ አድጌ በስራ አጋጣሚ ሳየው፥ የተለየ ስሜት እንደተሰማኝ አስታውሳለሁ። ላገኘው፥ ላየው የናፈቅሁት ዘመድ ወገን እንዳለ ያለ ስሜት። የማያቁት አገር አይናፍቅምን የሚያስተባብል ናፍቆት። ጥበብ ለማስተሳሰር፥ ለማስተዋወቅ፥ ለማነፋፈቅ አይነተኛ መላ መሆኑዋን የመሰከርኩበት አጋጣሚ።
የአድዋ ጦርነትን በፊት አውራሪነት የመሩት አፄ ምኒልክ፥ እቴጌ ጣይቱ፥ ፊታውራሪ ገበየሁ፥ ራስ አሉላ፥ ራስ መኮንንንና ሌሎች የጦር መሪዎች በኢትዮጵያ በኩል፣ በወራሪው ወገን ደግሞ የነበሩት ዋነኛ መሪዎች፣ እነ ጄኔራል ባሪያቴሪ፣ ፔትሮ ቶዞሊ ተጠቅሰዋል።
ሆኖም ታሪካዊ ክስተቱን ሳታጣርስ፥ በዘመን አግባብ ከፈጠረቻቸው ገፀ ባህርያት ጋር አዛንቃ ገድለኞች የምትለውን ህዝብ ዋነኛ የታሪኩ ማጠንጠኛ አድርጋ፥ በማይንገራገጭ ትረካ እነሆ ብላናለች። በእርግጠኝነት ይህንን ድርሰት አንብቦ ወይንም ትረካውን አዳምጦ በየትኛውም የአገሪቱዋ አካባቢ ያደገ ኢትዮጵያዊ፥ አፍሪካዊ ኩራት ያጎናፀፈውን የድል ቦታ በምናቡ ሊያየው እንደሚናፍቅ፥ መሰረቱንም ለመረዳት እንደሚተጋ አያጠራጥርም።
ወረኢሉን ይዘን፥ ደሴ ተሻግረን፥ አላማጣ አቅንተን፥ መቀሌ ቆይተን፥ ይሓ አኮብኩበን፥ አድዋ ላይ የድል አክሊል ተጎናፅፈን፥ አድዋን የከበቡትን አባ ገሪማን፥ ላዛትን፥ ኪዳነ ምህረትን፥ መንትኣ ገሰሶ ተራሮችን፥ ስንደዶን፥ ራዕዮን፥ እንባ መላዕክቲን፥ ገሊላን፥ ሰማያትን፥ ኤሻሾን፥ የኤራራና ሶሎዳ ተራሮችን ግዝፈት በምናባችን እየሳልን፥ ከምዕተ ዓመት በፊት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በነበራቸው ህብረት እንደመማለን። በጋራ መስዋዕትነት መዋደቃቸው፥ ለአገር ክብርና ድንበር የደም ዋጋ መከፈሉን እናሰላስላለን። በዚህ ድል የተገነባው ህብረት በቀጣይ አመታት ያጋጠሙንን ወረራዎች እንድንመክት መሰረት ስለመሆኑም እንመሰክራለን።
ሕይወት በዚህ ድርሰት ውስጥ፥ የጦርነት ዘመቻው ወቅት የነበረውን ሰብዓዊ ግንኙነት፥ ስነልቡናዊ አወቃቀርና በፍቅር መጋመድን ታሳይበታለች። የዘመን ስነልቡናና የሁኔታዎችን አረዳድ፥ የግለሰቦችን አስተሳሰብና ግጭቶችን በመተረክ ሰውኛ ሁኔታዎችን ትገልፅበታለች። የነበረውን ስብጥርና ለአንድ ዓላማ የተሰለፈ ህብረት ለማሳየት፥ የምግብ አይነቶችን በዝርዝር አስፍራልናለች። ቆንጠር አድርጋ ብዙ የአገራችንን ቋንቋዎችና ባህላዊ ጭፈራዎች ትጠቃቅስልናለች። በማሲንቆ በታጀበ ዜማና ግጥም እያሰናሰለች፥ ኩነቱን አዋዝታ ትተርክልናለች።
ገድሉን ለመፈፀም የተጠራው ሕዝብ ነው ብላ ከጅምሩ እንደገለፀችው፣ ለዚህ ዋነኛ ጭብጥ ማሳያ፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እግረኞችን፣ ዘመቻውን እያዋዛ ወኔ የሚቀሰቅስ አዝማሪንና ፈረሰኛ ገፀባህሪን ወክላልናለች። አንድ የታሪካዊ ልብወለድ ድርሰት፣ ከዘመናት በፊት የተከናወነ ታሪክን፣ ለዘመኑ አንባቢ እንደሚገባ አድርጎ ሊገልፅ ካልቻለ፣ አልተዋጣላትም ማለት ነው። “ተድባብ” ግን በታሪክ ያነበብነውን የአድዋ ዘመቻና ድል በገፀባህርያቱ በኩል ለዛ አላብሶ ስለሚተርክ፣ የተሳካለት ነው ማለት እንችላለን።
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከፍተኛ ሚና በአንድ የቤተክርስቲያን ሊቅ በኩል ወክላልናለች። በዚህም፣ ተራው ህዝብ በወኔ ቢነሳሳም፣ በአሉባልታና በአላዋቂዎች ወሬ ተነድቶ መስመር እንዳይስት፣ በዘመቻው ሂደት በሚካሄደው ውይይት፣ የአዋቂዎች (elite) አስፈላጊነትን ፍንትው አድርጋ ታሳየናለች።
በልጅነታቸው በአድዋ ጦርነት የተሳተፉት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በፃፉት ኦቶ ባዮግራፊ እንዲህ የሚል ምስክርነት አስፍረዋል።
“የሴቶቹን አገልግሎት ስገምት፥ ደግሞ የበቅሎዎቹ ይታወሰኛል። በመጨረሻም ድምሩን ስገምተው፥ የአድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና በበቅሎዎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል።” (ገፅ 57)
ሕይወት ተፈራም፥ የእቴጌ ጣይቱን ቆራጥና ብልህ አመራር ብቻ ሳይሆን፥ ሴቶች በጦርነቱ ያደረጉትን አስተዋፅዖ በሴት ገፀ ባህርያት ገልጣ ታሳየናለች።
ታሪካዊ ዳራውን ስትገልፅ የወቅቱን አለም አቀፋዊ ሁኔታና ሐያላን አገራት አፍሪካን ለመቀራመት የነበራቸውን ስምምነት፥ ጣልያንም የድርሻዋን ቅኝ ልትገዛ ኢትዮጵያ ላይ አይኗን መጣልዋን የሚያትት ነገር ከማስፈር ይልቅ፥ ደራሲዋ ታሪካዊ ዳራውን ከመቼቱ ጋር ለማጣጣም ገፀ ባህሪያትን መጠቀም ብቻ መፈለጓን እናስተውላለን። የአድዋው ድል አንዱ ትሩፋት፥ ፈር ቀዳጅና ቅኝ ገዢዎችን ያሳፈረ፥ የአፍሪካዊያን ኩራት መሆኑ ነው። እሷ ግን እዚያ ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ የጦርነትን አስከፊነትና ድልም መራራ መሆኑን ያስገነዘበችበት መንገድ ከሞራልና ሰብዓዊ ርህራሄ አንፃር ልትቃኘው ማሰቧን ያሳየናል።
በጦርነቱ በቀጥታ ተሳታፊ ባልሆነው አዝማሪው ይመር በኩል፣ የድል ጉሮወሸባዬን ሳይሆን፣ የሰውን ልጅ ከንቱ ፍንደለላና የጦርነትን አስከፊነት ምስል ትከስትልናለች። ሞራልን ደግሞ “ጣይቱ ተቆጡ። የሰው ልጅ ሬሳ ተለቅሞ ሳያልቅ ዕልልታው አበሳጫቸው” በሚል እምቅ አረፍተ ነገር እና ንጉሠ ነገሥቱን በማስለቀስ ዱብ ታረገዋለች።
“አገራችንን የምናድነው፥ በቅንነትና ይቅር በመባባል ነው” ብላ ማመኑዋ፥ ሕይወት ተፈራ “pacifist” ለመሆኑዋ ጠቋሚ ነው። ለዚህ ደግሞ “ማማ በሰማይ” ላይ በትግል ያሳለፈችውን መከራ አልፋ፥ ትግሉም እንደከሸፈ ስታውቅ፥ ፍቅረኛ (ጉዋደኛዋ) ጌታቸው ማሩ “የሰው ልጆች ሕይወት አንድን ሀሳብ ወደ ተግባር ከመለወጥ የበለጠ ክቡር ነው” ያለኝ አባባል “የተወልኝ መንፈሳዊ ቅርስ ነው” (ገፅ 365) ማለቷን እንደ አብነት መጥቀስ እንችላለን።
ሕይወት ተፈራ ቀጥሎ ይዛልን ስለምትመጣው ድርሰት እያሰላሰልን፥ ለእስካሁኑ “አምሃ ይገባሻል!” የምንላት፥ የልፋቷን ውጤት ገዝተን ስናነብ መሆኑን ባስታውስ ክፋት ያለው አይመስለኝም። መልካም ንባብ!
Digital/Audio Book Files
Br480.00