ለምንን ፍለጋ
A Book By - ቪክቶር ፍራንክል

In Stock
ለምንን ፍለጋ
Available Book Type
|
|
📗Printed
Book Info
Author - ቪክቶር ፍራንክል
Category - ስነልቦናዊ psychological
Translated Book - Yes
Language - Amharic
Translated From -English, English
Translated by - ቴዎድሮስ አጥላው
Number of Pages - 200
Book Review
መነሻ:- ድርሰትን መተርጎም የተለመደ እና የሚበረታታ ሲሆን፤ የትርጉም ሂደቱ ከዋናው መጻሕፍ ላይ ከቀጥታ ትርጉም (equivalent translation) ይልቅ በአገባብ/ በሁኔታ በመወሰን (contextual/ context-based translation) አንቀጽ-በአንቀጽ መተርጎም ይመከራል። ብሎም፣ የአንቀጾቹ ስብስብ (ወደ essay ከፍ ያሉ አንቀጾች) በessay መልክ ሲሆኑ የሚሰጡትን ትርጉም/ እንድምታ ማጤን ተገቢ ነው። ይህ ማለት አንቀጾቹ በessay ተጠቃለው/ተዋህደው የሚሰጡትን መልዕክት ከዋናው መጻሕፍ ፍሬ-ሀሳብ ጋር ማመሳከር አግባብ ነው እንደማለት ነው።
በትርጉም ሥራ ውስጥ፣ የመጀመሪያው (የዋናው) ድርሰት ማሕበረሰብ ታሪክ፣ ባሕል፣ ዕምነት… ወዘተ. የሚተረጎምለትን ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕል፣ ዕምነት… ሊጫን፣ ወይም ሊጣረስ ይችላል። ስለሆነም፣ ለሕዝቡ/ለአንባቢው ባመቸ መልክ (ዋናው ሃሳብ ሳይሸራረፍ) እየተኩ መተርጎም ይመከራል። እዚህ ላይ፣ ‹‹ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይብዛ›› የሚል የወንጌል ቃል፣ አሸዋ በሌለባቸው፣ በረዶ በመላባቸው አካባቢዎች ‹‹ዘርህ እንደ ምድር በረዶ ይብዛ›› ተብሎ ተተክቶ ተተርጉሞ አይተናል።
በአገራችን የተነበቡ የትርጉም ሥራዎች ከመጀመሪያው ድርሰት ላይ ትረካዎችን፣ ወይም የትረካ ክፍሎችን የመቆራረጥ/ የመሸራረፍ አባዜ ይታይባቸዋል። ይኼ ጉዳይ የድርሰቱን ሙሉ ሃሳብ እንዳንረዳው ያደርገናል። ለምሳሌ፣ ‹‹ፍቅር እስከ›› መቃብር ላይ የተተረከውን የሰብለንና የበዛብህን ውብ ጾታዊ መቧጠጥ/ንክኪ ቆርጠን ወደ ሌላ ቋንቋ ብንተረጉም የዚያ ቋንቋ ተናጋሪ የድርሰቱን ሙሉ ጭብጥ እንዳይረዳው ያደርጋል። የ‹‹ለምንን ፍለጋ›› በረከቶች:- “Man’s Search for Meaning”: – ትርጉም ድርሰቱ በጀርመን ውስጥ የነበረ የእስር ቤት ታሪክ ሲሆን፣ ባለ ታሪኩ (ቪክቶር ፍራንክል – የአዕምሮ ሕክምና ዶክተር ናቸው) ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር የነበራቸውን ቆይታ፣ ያሳለፉትን ፍዳ፣ ገጠመኞች…. ወዘተ. ያሠፈረበት ድርሰት ነው።
#ስግመንድ ፎሮይድ፣ ለአዕምሮ መታወክ መንሲኤው ከወሲብ ጋር በተገናኘ የሚከሰት ደስታ-ቢስነት ነው ይላል። ቪክቶር ፍራንክል ደግሞ፣ የአዕምሮ መታወክን ከፈቃድ ትርጉም (the will to meaning) ጋር ያያይዛል። ደራሲው ምንም እንኳን የግል የእስር ታሪኩን ቢያትትም፣ በዙሪያው የሚስተዋለውን የአዕምሮ ዝቅጠት (ለምሳሌ፣ በእስረኞቹ ዘንድ ሕይወትን ለማቆየት ሲባል ዝቅ ያሉ/ተራ የሆኑ ጉዳዮችን በማምሰልሰል፣ በማለም፤ ስለምግብና ስለመጠጥ አብዝቶ በመጨነቅ) የሚፈጠረውን የሥነ-ልቡና እና የሥነ-አዕምሮ ድቀት ፍቅረኛን በማለም፣ በጥበብ በመደሰት፣ የተፈጥሮ ጸጋን በማድነቅ፣ ጀንበርን/ብርሃንን በመናፈቅ፣ ውበትን በማድነቅ… ወዘተ. መቅረፍ እንደሚቻል ይገልጻል። ከአዕምሮ ዝቅጠት (mental regression) ለመላቀቅ (በአራዶች አባባል ‹ለመፋታት›) ፍቅር፣ ብርሃን፣ ውበት፣ ጥበብ፣ ተፈጥሮ… ወዘተ. አዎንታዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተገልጿል።
የምሳሌያዊ አነጋገር፡- በትርጉም ሥራዎች ላይ ትኩረትን ከሚሹ ጉዳዮች አንዱ የምሳሌያዊ አነጋገር ነው። በድርሰት ውስጥ አንድን ሃሳብ፣ ወይም ትረካ በምሣሌያዊ አነጋገር፣ በዘይቤአዊ ንግግር፣ በፈሊጥ፣ በተረት… መግለጽ ነገሩን ለማግዘፍ እና ግልጽ ለማድረግ ይረዳል። ተርጓሚው የምሣሌያዊ አነጋገርን የተጠቀመ ሲሆን፣ ይኼም ለአንባቢው ባሕል እና ልምድ በቀረበ መልኩ ነው። ለምሳሌ፣ ‹‹የተቸገረ እርጉዝ ያገባል››፤ ገጽ 21 ላይ መጥቀስ ይቻላል።የግርጌ ማስታወሻዎች፡- ይኼ ነጥብ የትርጉም ሥራው ልዩ መገለጫው ይመስለኛል። በትርጉም መጻሕፉ ውስጥ የተካተቱ የኅዳግ ማስታወሻዎች (በተርጓሚው የተጨመሩ)፣ አንድን ቃል ከማብራራት እስከ አንድን ርዕሰ-ጉዳይ በሰፊው እስከመተንተን ይደርሳሉ። የዚህ ፋይዳ በትረካው ውስጥ የተነሱ፣ ምናልባት ግርታን/ የግንዛቤ ችግርን ሊፈጥሩ ለሚችሉ ቃላትና ርዕሰ-ጉዳዮች አንባቢ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንዲያገኝ ይረዳል። ብሎም፣ የኅዳግ ማታወሻዎቹ ከዋናው የመጻሕፉ ጭብጥ ያፈነገጡ አይደሉም።
ለማሳያ፣ ገጽ 18፣ 22፣ 32፣ 35፣ 51፣ 78… ላይ በኅዳግ ማስታወሻ የተካተቱ ገለጻዎችን መመልከት ይቻላል። ይኼ ሙከራ እንደ አርአያ ተቆጥሮ ሌሎች ደራሲዎች በትርጉም ሥራዎቻቸው ላይ ቢሞክሩት ጠቃሚ ነው የሚል ሃሳብ አለኝ።የሙድ ዓይነት ጸሐፊ፡- አንድን ጉዳይ/ ታሪክ በቁመናው ልክ ከመዘክዘክ፤ በወቅቱ የነበረውን ሙድ መተረክ ለድርሰት ሀሳቡ ግዝፈትን ይሰጣል። ለአብነት ያህል፡- አንኮበር ተጉዠን የአጼ ምኒልክን ቤተ-መንግሥት እየጎበኘን ነው እንበል፤ ‹‹የንጉሠ-ነገሥቱን ሲናድር አይተን ተደመምን፤ ነካንም›› ከምንል ‹‹የንጉሠ-ነገሥቱን ሲናድር ለመንካት ተራኮትን›› ብለን ብንገልጽ ግዝፈት ይኖረዋል። ደራሲው፣ (ከሞላ-ጎደል) ታሪኮቹን/ገጠመኞቹን በሙድ ለመግለጽ ሞክሯል፤ በጊዜው የነበሩ ሁኔታዎች የጫሩበትን ሥሜቶች በምስል መልክ ተርኳል።
ምሳሌ እንጥቀስ፡- ‹‹የጠፈር አለንጋዎች እርቃን ገላዎችን ሲገርፉ ሰማን።…. ቀጥሎ ለመላጨት ወደ ሌላ ክፍል ተነዳን።›› ገጽ 28፤ በማለት የእስረኛውን ውርክብ እና የካፖዎቹን ያፈነገጠ አሠራር ተርኳል።
በሙድ የመተረክ ዘዬ፣ ዶ/ር ፍራንክልን የረዳቸው ይመስለኛል። የሥነ-ልቡና እና ሥነ-አዕምሮ ይዘት ያለውን ድርሰት በጊዜው በነበረው ሙድ ላይ ተመርኩዘው የእስረኞችን ሁኔታ፣ ችግርና መፍትሄ ለመተንተን ጠቅሟቸዋል የሚል ዕምነት አለኝ። እዚህ ላይ ሙድ/ሁኔታ ለአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መዘንጋት የለብንም። ሙዶች/ሁኔታዎች ጉዳይን የመገንባት/ ወደ-ጉዳይነት የማደግ አቅም አላቸው። የጉዞና የሥነ-ልቡና እንዲሁም የሥነ-አዕምሮ ድርሰቶች በሙድ መልክ ሲተረኩ ሃሳቡ ይገዝፋል ብዬ አምናለሁ። ደራሲው ከሙድ በመነሳት የተለያዩ መላ-ምቶችን ማስቀመጥ ይችላል።እዚህ ላይ የተርጓሚው ድርሻ የሚናቅ አይደለም፤ የትርጉሙ መልክ ታሪኮቹን በጥሬው መዶለት ሳይሆን፣ በጊዜው የነበሩ ሙዶችን/ሥሜቶችን በውብ ቋንቋ እያስደገፉ መተረክ ነው። እሰይ የሚያሰኝ ነው።
ንድፍ/methodology እና መቃን/ frame-work፡- በቀለም ትምህርት መስክ፣ ጥናታዊ ጽሑፍን ለማስኬድ ሁነኛ/ትክክለኛ ንድፍ፣ ብሎም መቃን እንደሚያስፈልግ ይታወቃል። ለአብነት፡- survey design, experimental design, correlational design, causal comparative/ex-post-facto design, case-study design… ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም፣ ንድፍና መቃን ድርሰትን በአግባቡ ለማስኬድ ይረዳሉ።
ለማሳያ፡- ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ልቦና፣ ሥነ-አዕምሮ… ወዘተ. በድርሰት ዓለም የተለመዱ ንድፍና መቃን ናቸው። ለጥቁምታ፡- ራሻዊያን ጸሐፊዎችን ብንመለከት፣ በድርሰቶቻቸው በሚስሉት ገጸ-ባሕሪይ በኩል የአንድን ፍልስፍናዊ ኅልዮት ሕልው መሆን፣ ወይም ውድቀት ለማሳየት ይሞክራሉ። ድርሰቱ በፍሬድሪክ ኒቼ ኅልዮት (theory)፣ ‹‹የሚኖርለት ለምን ያለው (ለ-ጠበቅ ተደርጋ ትነበብ) ሰው፣ ማንኛውንም እንዴት ይቋቋማል›› መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ ባለታሪኩ በኅልዮቱ ልክ ከከበበው ጨለማ ወደ ብርሃን ይሸጋገራል።
መውጫ፡- ‹‹ለምንን ፍለጋ›› ከታሪካዊ ዘገባ ይልቅ፣ የሙድ ጽሑፍ እንደሆነ ይሰማኛል። በትርጉም ሥራው ላይ በስፋት የተካተቱ የግርጌ ማስታወሻዎች ወገግታን ይፈጥራሉና ሌሎች ተርጓሚዎች ፈለጉን ይከተሉት እላለሁ። ከዚህ በዘለለ፣ ያለአግባብ የተጣመሩ ቃላት በትርጉም ሥራው ላይ ሠፍረዋል። (ጥምር ቃላት፡- ለምሳሌ ‹‹ሥጋ›› እና ‹‹ቤት›› የሚሉ ቃላት ሲጣመሩ – (ሥጋ-ቤት) – ትክክለኛ ፍቺ ያለው ቃል እንደሚፈጥሩ ይታወቃል፤ ነገር ግን በ‹‹ለምንን ፍለጋ›› ውስጥ በርካታ ቃላት ያለግብራቸው ተጣምረው ተገኝተዋል /ምናልባት በድንገት/። በንባብ ወቅት መታከትን ሊፈጥሩ እና ትርጉም ሊያዛቡ ይችላሉ። ‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ› ነውና፣ ይኼ ሃቲት ንጡል ሳይሆን፤ ዋናውንና ትርጉሙን ሥራ በወፍ-በረር የማየት ሙከራ ነው።
Digital/Audio Book Files
Br200.00