• ከመጽሀፍት ጋር ስሆን ከውጥረት አርፋለሁ፤ ከሁካታና ግርግር እጠለላለሁ፤ ብቻዬን ሆኜ በገፆች መስኮት ዓለምን እዞራለሁ። ዙሪያዬን እቃኛለሁ፣ ራሴን እመረምራለሁ፣ ከተሸናፊዎች ውድቀት እማራለሁ፣ ከአሸናፊዎች ጥንካሬን እላበሳለሁ። ከመጽሀፍት ጋር ስሆን ከብክነት እሰበሰባለሁ፣ ከጥፋትና ከክፋት እታቀባለሁ፣ ልቤ የፍቅር ቋንቋ ይሞላል። አንደበቴ በማር የተለወሰ ውብ ቃላትን ያፈልቃል። በዙሪያዬ እርጋታና ስክነት ይረባል። ይህ ስሜት የተለየ ደስታን ይፈጥርልኛል። ምቾት ይሰጠኛል። እናም ከመጽሀፍት ጋር ስሆን ዓለምን በእጄ የጨበጥኩ ያህል ይሰማኛል።