ለዚህ ነው ማንበብ የሚያስደስተኝ፣ አንባቢ ሰው የሚያስቅቀናኝ፣ መጽሀፍት የሚያጓጉኝ!!!
አንባቢ ሰው
አንባቢ ሲናገር አይደነቃቀፍም፤ ሃሳብ አይነጥፍበትም። እንዲያውም ቃላት ለሃሳቦቹ ይሰግዳሉ። ቋንቋ ይታዘዘዋል። የቃላት ሃብቱ ንግግሩ በጉጉት እንዲደመጥ ይጎተጉታሉ።
አንባቢ ሰው
ትልቅ የሃሳብ ጎተራ አለው። እውቀት በመልክ፣ በአይነት በአእምሮው ተሰድሯል። ስለ ማንኛውም ጉዳይ ቢያወራ፣ የሚናገረው ጠቃሚ ነገር አይጠፋም። ጆሮዎች ንግግሩን ለማድመጥ ወደ አንባቢ አፍ ይጠጋሉ። ንግግሩም ለጆሮ እንደ ማር፣ እንደ ውብ ሙዚቃ አይጠገቡም። መጻሕፍትን ያነበበ አንባቢ እውቀቱ ሰፊም፣ ጥልቅም ነው። አመለካከቱ በብዙ እሳቤዎች የተቃኘ ነው። እውቀቱ የደረጀ ነው። መሰረት አለው።
አንባቢ ሲጽፍም እንዲሁ ነው። የቃላቱ ፍሰት ተፈጥሯዊ ነው። ሃሳብ አይታገለውም። አይደነጋገርም። አይዋከብም። ልቡናእና አእምሮው ስሙም ናቸው—ሃሳብ ያፈልቃሉ፤ ስሜት ያመነጫሉ። ሃሳቡ እንደ ወንዝ ያለማቋረጥ ይፈሳል። ስሜቱ እንደ ፏፏቴ ይንፎለፎላል። ገባር ወንዞች ውሃ አዋጥተው ዋናውን ወንዝ ግዙፍ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አንባቢው ከብዙ መጻሕፍት የቃረመው እውቀት ሃሳቡን ያገዝፈዋል።
እናም ሰው ካነበበ ያስተውላል። በመቶ የሚቆጠሩ አዳዲስ እውቀቶች፣ አዳዲስ ልምዶች ይኖሩታል። የንባብ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ አለምን በስነጽሑፍ ይዞራል። በማንበብ ብቻ ምናቡን ያሰፋል። በሌሎች ውስጥ ራሱን ያገኛል። ታላላቅ ደራሲዎች ስለራሱ ጠቃሚ እውነቶች ይነግሩታል። ወደ ራሱ እየጠለቀ ይመጣል። እዚያ በሚያገኘው ነገር ይደነቃል። ከአልማዝና ወርቅ የከበረ ነው። የራሱን ቀለም፣ የራሱን ድምጽ፣ የራሱን ቋንቋ ያገኛል። ምንጭ TeDi
ለዚህ ነው ማንበብ የሚያስደስተኝ፣ አንባቢ ሰው የሚያስቅቀናኝ፣ መጽሀፍት የሚያጓጉኝ።
Responses