ቀይባህር ሲቀላ
A Book By - ዶር ፍርድአወቀ ማሞ
In Stock
ቀይባህር ሲቀላ
Available Book Type
|
|
📗Printed
Book Info
Author - ዶር ፍርድአወቀ ማሞ
Category - እውነተኛ ታሪክ
Translated Book - No
Language - Amharic
Number of Pages - 400
Book Review
ቀይ ባሕር ሲቀላ ~
የዶ/ር ፍርድአወቀ ማሞ እውነተኛ ታሪክ
#Ethiopia | ዶ/ር ፍርድአወቀ ያገለገለበት እኔም ለሦስት ዓመታት የሠራሁበት ሆስፒታል የአንድ ግቢ ተጎራባች ነበሩ። እነርሱ ሲቪሉን ማኅበረሰብ እኛ ደግሞ ባሕርተኞቹን ስናክም ኖርን። የ1982 የካቲቱ የምፅዋ ጦርነት ግን አንድ አደረገን። ጠቅልለን አብዱል ቃድር ባሕረ ሰላጤ ላይ ከተምን እና በሺሕ የሚቆጠሩ ቁስለኞችን ማከም ቀጠልን። ለጥቂት ቀናት ባልደረቦች ሆንን። የቀረው ታሪክ ነው። የደራሲው ማስታወሻ የከተባቸውን ቦታዎች ከሞላ ጎደል ረግጫቸዋለሁ። ምልከታው ምልከታዬ ስጋቱም ስጋቴ ነው። ከእርሱ በላይ የሚያባንነኝ ትዝታም ሞልቶኛል። ያ ጦርነት ሁሉም ኃይሎች (የምድር፤ የአየርና ባሕር) የተሳተፉበት ብቸኛው ነው። ከዚያ በፊት አልሆነም። አልፎም አልተደገመም።
የቶሪኖ፣ ዳንሰ ማርያና ዓለምብራ ሙዚቃ በ“ስታሊን ኦርጋን” ሲተካ ዕጣ ወድቆብኝ እዚያው ነበርኩ። በጭንቅ ቀን ከሆስፒታል ጀርባ 120 ሚ.ሜ መድፍ ሲጠመድና ሲያጓራ፣ በኮምዩኒዝም ፍልስፍና አምላኩን የረሳ ዜጋ “የዛሬን” እያለ ሲጸልይ በጆሮዬ ሰምቻለሁ።
የሰሜን ቀይ ባሕር ዕዝ ሕንፃ እንደ ደመራ ዛፍ የተገነደሰው አጠገቡ ቆሜ ነበር። ሲሚንቶ ፋብሪካው በፓራሹት የሚወርድና በርሜል የሚያህል ቦንብ ወድቆበት ከፍንዳታው ድምፅ የተነሣ ምድሪቱ ስታቃስት አብሬ ቃትቻለሁ። የአጂፕ ነዳጅ ማከማቻ ተመሳሳይ ጡጫ ሲቀምስ አገሩን ያለበሰ ታላቅ ጢስ ሲወጣ እንደ ፊልም አፍቃሪ ፈዝዤ አየው ነበር።
ከወዲያ ማዶ የተላከ ቅንቡላ ካረፈበት አዳራሽ ተገኝቼ ቁስለኞች በተኙበት እንደ ጧፍ እየነደዱ እንደ ሻማ ሲቀልጡ ደርሼ የጨው ዐምድ ሆኛለሁ። ጊዜ ባልነበረበት የወደቁ ወዳጆቼን ፊት በጨርቅ በመሸፈን “የክፉ ቀን ቀብር” አከናውኛለሁ። ምስክር እሆን ዘንድ መልካሚቱ የአምላኬ እጅ ከልላ ዳር ብታወጣኝም ዋናተኞች አናታቸው እየተፈረከሰ ሰማያዊው ውኃ ወደ ደምነት ሲቀየር ዐይቻለሁ።
“ቀይ ባሕር ሲቀላ” ያንን የአእላፋት እልቂት መታደግ አልተቻለውም። ያ እንዳይደገም ግን ሰሚ ቢገኝ ብሎ ይመክራል። የደራሲው ጩኸት በትክክል ተሰምቶኝ ከሆነ “የተሻለ አማራጭ አለ፤ ጦርነት ለችግራችን መፍትኼ አይሆንም!” ነው የሚለው። እስማማለሁ። ጸሐፊው የጦርነቱን አንድዋን ሰበዝ በብዙ ገፆች መዝዞ ትልቅ ጥያቄ አቅርቦልናል።
መተላለቁ ምን ፈየደ? መልሱ ምንም ይሆናል። “እንውጣ፣እንዋጋ” እያለ ብዙ ቀንበጦችን ያስቀጠፈው እርሱ ግን ቀድሞ የተማረከው ካድሬም ይሁን አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር ለመዋጋት ያልሙና ይምሉ የነበሩት ወታደራዊ መሪ በዚህ የሚስማሙ ይመስለኛል። ይነበብ።
ዓለማየሁ ማሞ (ደራሲና ጋዜጠኛ- ሜሪላንድ/ አሜሪካ)
***
አባቱ እገዛ ጓሮአቸው በቦምብ ፍንጣሪ ፈስሶ እልቆ፣ ነፍሳቸው እስክትወጣ ቆሞ ተመትተው ፤ ደማቸው ከማየት በቀር አንዳች ማድረግ ስላልቻለው ምስኪን ታዳጊ ወጣት፤ ሆቴል ቤት ተቀጥራ የቀረችባቸው ዘመድ የለሽ ድኃ እሮጊት ፤ በፍቅር ፣ ሠላም፣ ቤተሰባዊነት፣ መከባበር፣ ሳቅና የተፈጥሮ ውበት የደመቀችው የምፅዋ ከተማ ወደ ፍርስራሽነት ጣረሞት ስትለወጥ፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና አዛውንት ካለቁ በኋላ የጦርነቱ ፍሬ ከንቱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፣ ወደፊት ሌሎች ጦርነቶችን የሚወልዱ መለያየቶችንና ቂሞችን እንደፈጠረ፤ … ልብን በሚያርድ፣ አጥንትን በሚያቀልጥ አፃፃፍ ያቀርብልናል።
“ምፅዋ እሳት ወረደባት። የሃያኛው ክፍለ ዘመን ሰዶምና ገሞራ ሆነች።… የፌሽታዋ ምድር ምፅዋ፣ የተቀዳደደች የለቅሶ ድንኳን መሰለች” ይለናል። ከአራት መቶ በላይ ገፆችን በሚገልጠው መፅሐፉ፣ “ጦርነት የችግራችን መፍትሔ አይደለም!” የሚለው የደራሲው መልዕክት በጉልህ ይስተጋባል፡፡ ይልቁኑ መነጋገርን ፣ መደማመጥን እና ሰጥቶ መቀበልን እንድንመርጥ በትሕትና – ይመክረናል። በሌላ በኩል ፣ ከዚህ ሁሉ መቋሰል በኋላም የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሚለያየን ይልቅ የሚያቀራርበን ይበልጣልና፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን እንድንመርጥ ይመክረናል፡፡ በጎነት ከከፋት ፣ ብርሃንም ከጨለማ እንደሚያይል ተረድተን የበጎነትንና የብርሃንን ሠራዊት እንድንቀላቀል በፍፁም ትሕትና እና ቅንነት የቀረበልንን ይህንን ምክር ብንሰማ ይጠቅመናል።
ፓስተር ምኒልክ ታምራት
***
ዶ/ር ፍርድአወቀ ማሞ የታሪካችንን ጨረፍታ በወፍበረር በሚመስል፣ ግን በጥልቀት በተረከበት “ቀይ ባህር ሲቀላ” ውስጥ ይጠይቃል። “ምን ዓይነት ጣጣ ነው? ታታሪ ዜጎች ለፍተው ባመጡት ዕድገትና ለውጥ፣ መሪዎቻችን ይወደሱበታል። አርቆ ማሰብ በማይችሉ መሪዎች በሚደርሱ ጥፋቶችና ውድመቶች ደግሞ፣ ምንም እጁም ሃሳቡም የሌለበት፣ እነርሱ እንመራሃለን የሚሉት ዜጋ ይወቀሳል፤ ይሰደባል ፤ ይሰደዳል ፤ ይገደላልም። ” ይላል። የዶክተር ፍርድአወቀ ማሞ አስደማሚ ትዝብት ያልዳነው እና ያልተፈወሰው ታሪካችንን እና ከግጭት መፋታት ያቃተውን መስተጋብራችንን ያትትልናል።
በአስጨናቂውና ወሳኙ የምጽዋ ግንባር ጦርነት እንደሃኪም ተዋናይ፣ የሁለቱም ማኅበረሰብ ስነልቦና ተሰርቶ እንዳደገ ሚዛናዊ፣ ጥልቅ ትዝብቱን እና የታሪክ ምስክርነቱን፣ እንደሰለባ ከሞት ጋርበየዕለቱ የተፋጠጠበትን እና የዘመናት የሰላም ቃተቶውን የታሪክማስታወሻ አስቀምጦልናል። ”ቀይባህር ሲቀላ’ን ከጀመርኩት በኋላ ሳላቆመውና ሌላ ነገር ጣልቃ ሳላስገባ እንድጨርሰው አስገድዶኛል። ”ቀይ ባህር ሲቀላ” ጦርነት ባቆሰለው ስሜታችን ላይ የሚፈስ የማስተዋል ዘይት ነው።
ኦሃድ ቤንአሚ
***
ሰማያዊው ውኃ ወደ ደምነት ሲቀየር ዐይቻለሁ፡፡
‘ቀይ ባሕር ሲቀላ” ያንን የአእላፋት እልቂት መታደግ አልተቻለውም፡፡ ያ እንዳይደገም ግን ሰሚ ቢገኝ ብሎ ይመክራል። (ገፅ 400)
ዓለማየሁ ማሞ (ደራሲና ጋዜጠኛ- ሜሪላንድ/
Digital/Audio Book Files
Br750.00
