ከአእምሮ ምግብነት ባሻገር
የተሻለች አገር ለመፍጠር የተመረጡ መጻሕፍትን በየትኛውም ሰዓትና ቦታ ማንበብ ከአእምሮ ምግብነት ባሻገር የተሻሉ መሪዎችን ለማውጣትና የበለጸገች አገር ለመስራት አቋራጭ መንገድ ነው ። ዓለም ላይ የተዋጣላቸው መሪዎች ብዙ ዲግሪ ያላቸው ሳይሆኑ እጅግ አንባቢዎቹ ናቸው ። ከአሜሪካው ቴዎዶር ሮዝቬልት እስከ ቻይናው ማኦ ሴቱንግ ፣ ከሌኒን እስከ ፑቲን ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪ መሪዎች እጅግ አንባቢዎች ናቸው ። በሌሎቹም የዕውቀት መስክ ተጽእኖ ፈጣሪዎቹ አንባቢዎቹ ናቸው ።
የሚያነብ መሪ ፣ የሚያነብ ፓለቲከኛ ፣ የሚያነብ አለቃ፣ የሚያነብ አስተማሪ ፣የሚያነብ አክተር ፣የሚያነብ ደራሲ ፣ የሚያነብ አባት ፣የሚያነብ ተመራማሪ ፣ የሚያነብ ሰባኪ ፣ የምታነብ እናት ሥልጡን ሕዝብና የሠለጠነች አገር ለመፍጠር የማእዘን ድንጋይ ናቸው ። ያው የሚያነብ ሰው የተሻለ አስተሳሰብ ሳያዳብር አይቀርምና ….. የነቃና ተራማጅ ሕዝብ ቆፍጣና መሪዎችንና ሳይንቲስቶችን ይወልዳል።
የኢትዮጵያ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ብዛት ያለው የነቃ ተራማጅ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው ። አንድ ጠቃሚ ሃሳብ እንኳን ይዞ የመጣን ብርቱ ሰው ሃሳቡን መረዳትና መግዛት የሚቻለው በተለያዩ መጽሐፍት የተሞረደ አሰላሳይ ንቁ ሕዝብ ሲኖር ነው። እኛም የካርል ማርክስን “ዳስ ካፒታልን” ፣ የአየን ራንድን ” (አትላስ ሽረግድን) ፣የዶስቶቪስኪን (ዘ ካራማዞቭ ብራዘርስን)፣ የዮቫል ኖኅ ሀራሬ መጽሐፍቶችን ፣ከነ አዳም ስሚዝ (የአገራት ብልጽግና ) እስካሁን ያሉት የምጣኔ ኃብት መጽሐፍቶችን ፣ የቴክኖሎጅ መጽሐፍቶችን፣ ጠንካራ- የስነ ልቦና ፣ የስነ-መለኮት ፣ የስነ-ጥበብ፣ የፍልስፍና ፣ የስነ ምግባርና ሌሎች የማናውቃቸውን አያሌ መጽሓፍቶችን ከውጭ ቋንቋ ወደ አገር ውስጥ ቋንቋ በመተርጎም ማንበብና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አለብን !
Responses